ጾመ ነቢያት
ዘመኑ ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡ ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡
ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር «የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡
ዘመነ ስብከት
ከታኅሣሥ 7 ቀን እስከ ታኅሣሥ 13 ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት ናቸው፡፡ ምን ጊዜም ወደ ታኅሣሥ 6 አይወርድም ወደ 14ም አይወጣም፡፡ ስብከት ማለት ዐዋጅ ትምህርት ማለት ነው፡፡ ይህም ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ያለው ትውልድ የሚታሰብበት ፤ ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያት በትንቢት፣ ዳዊት በመዝሙሩ በብዙ ምሳሌ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ የተናገሩት የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ መዝ.143-7 ፤ ኢሳ 64-1፡፡ የሚዘመረው መዝሙር «ወልደ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፤ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን» የሚል ነው ቅዱስ ያሬድ፡፡ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለትንና ሱባዔ የቆጠሩለትን ሐዋርያት ያላቸውን ትተው ተከተሉት ፈቃዱንም ፈጸሙ፡፡ ስለዚህ ምእመናን ክፉ ሐሳባቸውን አርቀው ርኩሰትን አስወግደው ፍጹም ለእግዚአብሔር እንዲገዙ ትምህርት ይሰጣል፣ ስብከት ይሰበካል፡፡ የሚነበበውም ምንባብ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ ዮሐ.1-44-49 ፤ ዕብ.1-1-2፡፡
ብርሃን
ከስብከት ቀጥሎ ያለችው ሰንበት ስትሆን እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተምህሮ ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ያለው 14 ትውልድ ይታሰብበታል፡፡ ክቡር ዳዊት «አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42-3/ እያለ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ወገን እንዲወለድ ትንቢት ስለተናገረ ይህ የሚታሰብበት ነው፡፡ ነቢዩ ዓለም በጨለማ ስለሆነች ብርሃንህን ላክ፣ ሐሰትና የሐሰት አባት ነግሦባታልና እውነትህን ላክ አለ፡፡ ወልድን ላክልን ማለቱ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ዮሐንስ «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» ብሎ ሲመሰክር ጌታም ራሱ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም» ብሎ ተናግሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 8-12 እንዲሁም ብርሃንን እውነት ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ላክልን ሲል ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ስደድልን ማለቱ ነው፡፡
ከጨለማ ወደ ብርሃን አውጣን፣ ሥጋህንና ደምህን ስጠን ሲልም ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩት መዝሙራት «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ወይዜንዎ ለጽዮን በቃለ ትፍሥሕት፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፣ የምስጋናን ቃል ለጽዮን የሚነግራት ወልድ በክብር፣ በጌትነት እንደሚመጣ አስቀድሞ በኦሪት ነገረ፤ አስታወቀ፡፡» የሚሉ ናቸው፡፡ ንስሐ ከመግባት ቸል እንዳይሉ ይነግራቸዋል፡፡ ነቢያት የጥል ግድግዳን ሰብሮ መለያየትን አጥፍቶ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣቸውን ሽተው ውረድ ተወለድ አድነንም እያሉ ጮኹ፣ እውነተኛ ብርሃን ጌታችን ጊዜው ሲደርስ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ በመምጣቱም በጨለማ ያለው በብርሃን እንዲገለጥ ለሰው ልጆች እግዚአብሔርን የሚያውቁባት ዕውቀት ተሰጠች፡፡
ኖላዊ
ኖላዊ ተብሎ የሚጠራው ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ነው፡፡ የቃሉ ፍች እረኛ ማለት ነው፡፡ እረኞች ለበጎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሣር ውኃ ሳያጓድሉ እንዲጠብቁ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ ነው፡፡ ይኽንን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲያብራሩ ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው 14 ትውልድ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ዘመን እሥራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በባቢሎን 70 ዘመን ከኖሩ በኋላ ዘሩባቤልን አንግሦላቸው ይዟቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በፊት እሥራኤል ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ተበታትነው ሲኖሩ ነቢያት ከኪሩቤል ላይ የሚገለጥ እረኛቸው እንዲገለጥ የእሥራኤል ጠባቂያቸው ሆይ፣ አድምጥ እያሉ የጠየቁበት መታሰቢያ ነው፡፡ መዝ.79-1-3፡፡
መዝሙሩም «ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃለ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ» የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ ዮሐ.10-1-22፡፡ እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር» እንዳለ፡፡ 1ኛ ጴጥ.2-25፡፡ ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡
ገሃድ/ ጾመ ድራረ ጥምቀት
ይህ ጾም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በማሰብ የጥምቀትን ዋዜማ መጾም ነው፡፡ ይህም ማለት በጥምቀት ዋዜማ ከምግብ መከልከል ነው፡፡ የሚቆርብ ሰው አክፍሎ የሚያድር ስለሆነም የጥምቀትን ድራር መጾም ነው፡፡ ሐዋርያት «ልደት ጥምቀት ዓርብ ረቡዕ ቢውል በሌሊት ቀድሰው ሥጋውን ደሙን ይቀበሉ፤ ከሌሊቱ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ብለው አይፍረዱ» ብለዋል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15/፡፡ የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት ምግብ በጠዋት በመብላት ምእመናን በዓሉን እንዲያከብሩ ታዟል፡፡
ይህም እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ የእግዚአብሔር በዓላት በመሆናቸው ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ በሚውልበት ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ ማክሰኞንና ሐሙስን በመጾማችን ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል፡፡ በዚህም የጾምና የበዓል ማክበር ሥራ ይከናወናል፡፡ የጥምቀትን ዋዜማ ጥሉላት መባልዕትን መተው ነው፡፡ ይህንንም እንደ ዘይቤው ገሀድ ይለዋል፣ መገለጫ፣ ግልጥ፣ ይፋ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ጋድ ይለዋል፣ ለውጥ፣ ልዋጭ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ረቡዕ ዓርብ ሲውል በዚያ ለውጥ ማክሰኞ ሐሙስ ይጾማልና ጋድ አለው፡፡ እንዲሁም አንድ ጊዜ ሲጾም አንድ ጊዜ ሲቀር እንዳይረሳና ቅዳሜ ወይም እሑድ በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ አይቻልም፣ ነገር ግን እህል ውኃ እንጂ ጥሉላት ከመብላት መጠበቅ ይገባል፡፡
ልደት የሚውልባቸው ረቡዕና ዓርብ ቢሆኑ የፍሥክ /የሚበላባቸው/ ቀናት ሆነው እንዲከበሩ ሐዋርያት ያዘዙ ቢሆንም በዋዜማው የሚገኙት ማክሰኞና ሐሙስ ከጾመ ነቢያት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ መጾማቸው ግድ ነው፡፡ ሆኖም የነቢያትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች በመላው የጾሙ ቀናት ሲበሉ ቆይተው በዋዜማው ብቻ ገሀድ ነው ብለው ይጾማሉ፡፡ ነገር ግን ለጾመ ነቢያት ገሀድ የለውም፡፡ ጾሙ የጥምቀት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለጾመ ነቢያት ገሀድ እንዳለው የሚናገሩም አሉ፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ እስከ ምሽት መጾሙን ነው፡፡ ይህም «አድልው ለጾም፤ ለጾም አድሉ፡፡» እንዲሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቢጾም የሚያከራክር ወይንም ስህተት ነው የሚያሰኝ አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው የተናገሩት ቃል ይፈጸም ዘንድ የሰው ልጆችም ድኅነት ማረጋገጫ እውን ይሆን ዘንድ እንደ ጾሙ እንደ ጸለዩ በልደቱም እንስሳት፣ ሰዎች እንዲሁም መላእክት በአንድነት በደስታ እንደዘመሩ የእኛም ደስታ የተረጋገጠበት ነው፡፡ በመሆኑም በፍቅር፣ በጾም በጸሎት ዛሬም እናስበዋለን፡፡ ነቢያት በረከት እንዳገኙ እኛም ከእግዚአብሔር በረከት እናገኛለን፡፡ ለዚህም አምላካችን ይርዳን አሜን፡፡