Top

Contact Us

Use the form on the right to contact us.

You can edit the text in this area, and change where the contact form on the right submits to, by entering edit mode using the modes on the bottom right. 

(416) 781-4802

About Ethiopian Orthodox Tewahedo Church
--------------------------------------------------------------

Ethiopia, the land of Judeo-Christianity, is one of the most ancient predominantly Christian countries of the world. It is marked with a fascinating history, unique civilization, culture and religious life. The Book of Genesis recounts: “And the name of the second river is Ghion: the same is it that compasses the whole land of Ethiopia” (Geneses 2:13). The Psalmist David also says: “Let Ethiopia hasten to stretch out her hands to God” (Psalms 68:31).

የቤተክርስትያናችን ታሪክ


 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ።

ኢትዮጵያ የጁዲዮ የክርስትያን እምነትና ባሕል ያላት ጥንታዊት አገር ስትሆን የክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት የሚግኙባት ነች። አስገራሚ ታሪክ፣ ድንቅ ሥልጣኔዋ፣ባሕልና ሃይማኖታዊ የሆነው የሕዝቧችዋ አኗኗር ልዩ ያደርጋታል። በኦሪት ዘፍጥረት እንደተጻፈው “የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፣እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።” (ዘፍ. 2፥13) በዳዊት መዝሙር ደግሞ “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” (መዝ. 67(68)፥31)። ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ በብዙ የታሪክ መዛግብትና መጽሐፍት ላይ ስለ ኢትዮጵያ ተዘግቧል። በተጨማሪ ታሪካዊና አርኬኦሎጂካል ግኝቶች የሚያስገርሙ ሃቆችን ስለ ኢትዮጵያ እየገለጹ ነው። ኢትዮጵያ የራስዋ የሆነ ፊደል ከነአጻጻፉና ሥርዓቱ ጋር ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ነች።

 

ጥንታዊ የግሪክ ባለ ቅኔዎች፣ ገጣሚዎችና የታሪክ ጸሐፊዎች ስለኢትዮጵያ ብዙ ጽፈዋል፤ ከነዚህ መካከል ሆሜር ስለአገሪቱና ስለሕዝቧ ሲገልጽ “እንከን የሌለባቸው ዘሮች” ሲል ሔሮዶቱስ ደግሞ የኢትዮጵያን የመልክዐ ምድር አቀማመጥን እንዲህ ሲል ገልጾታል፣ “ከግብፅ በስተደቡብና የቀይ ባሕር አካባቢን ይዞ እስከ ሕንድ ወቂያኖስ የሚጠጋ ግዛት ነው” ስለሕዝቧም ሲናገር “የረጅም እድሜ ባለፀጎችና እውነተኛ የሆኑ ሕዝቦች ናቸው”ብሏል።

 

በብሉይ ኪዳን ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰለሞንን ለመጎብኘት ወደ የኢየሩሳሌም ያደረገችውን  ጉዞ በ1ኛ ነገ. 10፥1-13 ተጽፎ ሲገኝ በኢትዮጵያውያንም ዘንድ ይህ ጉዞ ብሉይ ኪዳን በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ያደረገና፤ የንጉሥ ሰለሞንና የንግሥት ሳባ ልጅ የሆነው ቀዳማዊ ምኒሊክ ጽላተ ሙሴን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ያደረገ ነው ተብሎ ይታመናል።

ከዚያን ጊዜ በኋላ የአይሁድ እምነትና ሥርዓተ አምልኮ የሕዝቧ እምነትና የቀን ተቀን ኑሮ መመሪያ ሆኗል። በቀዳማዊ ምኒሊክ የተመሰረተው የአክሱም ሥርወ መንግሥት ተብላ ትታወቅ ነበር። በተጨማሪ ብዙ የታሪክ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በኢትዮጵያ ነፃ መንግሥት የተመሰረተው ከ 4,522 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። የዛሬይቱ አክሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ዋና መዲና፣የሥልጣኔ መገኛና የክርስትና እምነት መወለጃ እንደሆነች ዛሬ የሚታዩት የሕዝቧ ኣኗኗርና ሃይማኖታዊነት፣ ታሪካዊ ቅርሶችዋ፣የቆሙት ሐውልቶችዋና ልዩ ልዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎቿ ሲመሰክሩ አክሱም አሁንም ዋነኛ የሃይማኖት መንጸባረቂያ ቅድስት ቦታ ነች።

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሊቃውንቶችና የተማሩ ቀሳውስቶች ያላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከሰላሳ ሺህ በላይ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ቀሳውስቶችና ወደ አርባ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ያላት አገር ስትሆን በዚህም ከምሥራቃውያን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ አገሮች በምዕመናን ብዛት የቀዳሚነትን ሥፍራ ይዛለች።

ለተጨማሪ ታሪካዊ ማስረጃዎችና ስለ ቤተ ክርስትኗ ታሪክ ለመረዳት የሚከተሉትን መጽሐፍቶችና ሌሎችንም ይመልከቱ፣

Martin Bernal: Black Athena (1987), Henry Hill: Light from the East (1988), Arch Bishop Yesehaq: The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church (1975) and Stanslaw Chojancki: Ethiopian Icons.


 

በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት አመጣጥ።

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ዘመን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና ሌሎች ታሪካዊ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። (ሐዋ. 8፥26-36) ላይና በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳቢዮስ “የኢትዮጵያው ጃንደረባ ጥምቀት በዓለም የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬ” ብሎታል በተጨማሪም ሩፊኖስ ቀጥሎም በቴዎድሬት፣ሶቅራጦስና ሶዝሜን ታሪክ ዘጋቢዎች ይህንን ታላቅ ሁኔታ ዘግበውታል። ይሁን እንጂ ክርስትና የመንግሥት እምነት ሆኖ በኤጲስ ቆጶስ ደረጃ መመራት የጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይተረካል። ይኸውም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ፍሬሚናጦስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አድርጎ የሾመው በዘመነ አብርሃና አፅብሃ ጊዜ ነው። ንጉሥ ኤዛና በገንዘቦቹ ላይ የነበሩትን የጨረቃ ሥዕልን ቀይሮ የመስቀል ምልክት በማድረግ በዓለም ከነበሩት ነገሥታቶች  መካከል ቀድምትነትን ቦታ አግኝቷል። በ356 ዓ.ም.  አርያናው ንጉሥ ኮንስታንትዩስ ለአክሱም ንጉሥ ሲጽፍ “ጳጳሱ ፍሬሚናጦስ የክርስትናን እምነት አጥፊ ስለሆነ ወደ ሮም ተይዞ ይላክ” ብሎ ነበር። ነገር ግን ይህ ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝለት ቀርቷል። ቅዱስ ፍሬሚናጦስ በኋላ በኢትዮጵያውያን ኣባ ሰላማ (የሰላም አባት) ከሳቴ ብርሃን (የብርሃን ገላጭ) እየተባለ ሲታወቅ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የጳጳሳት መጠሪያ የሆነውን አቡን የሚባለው አጠራር ማለትም (አባታችን) ተቀብሎ ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ብቻ ትቀበላለች እነርሱም የኒቅያው ጉባኤ (325 ዓ.ም.) የኤፌሶን ጉባኤ (381 ዓ.ም.) የቁስጥንጥንያ ጉባኤ (431 ዓ.ም.) ናቸው። ስለዚህ ሁለቱ ጉባኤዎች ያወጧቸው ጸሎተ ሃይማኖትን ተቀብላለች። ይኸም እንደ ሚከተለው ነው፣

         

“ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር እናምናለን።

ዓለም ሳይፈጠር ከርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ   በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን።

ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደል የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።

ሁሉ በርሱ የሆነ ያለ እርሱ ግን ምንም የሆነ የለም። በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።

ስለእኛ ስለሰው ስለ መዳኛችን ከሰማይ ወረደ። ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።

ሰው ሆኖ በጰንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ። ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረም፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጽሐፍት እንደ ተጻፈ።

በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ዳግመኛ ሕያዋንን ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥስቱም ፍጻሜ የለውም።

ጌታ ማሕየዊ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ፤ ከአብና ከወልድ ጋር በነብያት የተነገረ።

ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን።

ኃጥያትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት አናምናለን።

የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን።”

 

የዘጠኙ ቅዱሳን (ተሰዓቱ ቅዱሳን) ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል። እነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳት በመባል የሚታወቁት ከወደ ቢዛንታይን ሥርወ መንግሥት በ479 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ይነገራል። እነርሱም የሕዝቡን ቋንቋ ግዕዝን ተምረው ባሕሉን ተምረው መጽሐፍ ቅዱስንና ብዙ የተለያዩ መንፈሣዊ  መጽሐፍትን ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክና ከሲሪያክ ቋንቋዎች ወደ ግዕዝ ቋንቋ ተርጉመዋል፣ ወንጌል ከመስበካቸው በተጨማሪ ክርስቲያናዊ ገዳማትን በማቋቋም ገዳማዊ ሕይወት እንዲመሠረት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ የተሸጋገረችበት ወቅት ነበር። ይሄውም ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያንን ዜማ፣ቅኔና ዝማሬን አዘጋጅቶ ከአገልግሎት ላይ እንዲውል ያደረገበት ወቅት ስለነበረ። በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲይኗ ከፍተኛ እድገት የታየባቸው ዘመኖች ከ4ኛ እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ያሉት ወርቃማ የቤተ ክርስቲያን የእድገት ዘመኖች በመባል ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያ በመካከለኛው አፍሪካ የክርስትና እምነት ማዕከል በመሆን የምትታወቅና የራሷ የሆነውን የክርስትና እምነቷንና ታሪኳን የጠበቀችና የነፃነት ምልክት በመሆን ለዘመናት ሁሉ የቆየች አገር ነች።


 

ምንኩስናና ገዳማት በኢትዮጵያ።

ክርስቲያናዊ የሆነ ገዳማዊ ኑሮ በኢትዮጵያ ማበብ የጀመረው የክርስትና ሃይማኖት የአገሪቱ ብሔራዊ እምነት ሆኖ በነገሥታቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው። የግብፃዊው የቅዱስ አንጦኒዮስን ገዳማዊ ሥርዓት የተከተለ በ 479 ዓ.ም. ወደ ሀገሪቱ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን አስፋፍተውታል።

ስለዚህ ነው ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ ወርቃማው ተብሎ የሚታወቀው። በነዚህ ዘመናት ውስጥ ብዙ የስብከት ወንጌል ሥራዎች ተስፋፍተዋል፣ ልዩ ልዩ መንፈሣዊ ሥራዎችና ጽሑፎች የተከናወኑበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ ያሉ ገዳማት የምዕራባውያንን ባሕል በመካከላለኛው ክፍለ ዘመን እንዲስፋፋና እንዲጠበቅ እንዳደረጉት ሁሉ በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትም የእውቀትና የሥልጣኔ ማዕከል በመሆን ሥነ ጽሑፎችን፣ ሥነ ሕንፃን፣ ቅኔዎችን፣ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችንና መንፈሣዊ ትምህርቶች እንዲዳብሩ አድርገዋል። በ5ኛው ክፍለ ዘመን የታወቀው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የቅድሴ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችንና ውዝዋዜዎችን በመፍጠር ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይህ ለጆሮ ክፍተኛ ጣዕም ያለውን የምስጋናና የጸሎት ሥርዓት ያላትና የምትጠቀም በዓለም ያለች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን አድርጓታል።


 

መጽሐፍ ቅዱስ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደምታምነው “ከጥንት ጀምራ እንደጊዜው ሁኔታና ሕዝብ አኗኗር ሁሉም በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም ትምህርትና ዕውቀት እንዲያድግ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆኑትን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ነው።”

ቤተ ክርስቲያኗ የምትቀበላቸው የቀኖና ቅዱስ መጽሐፍት 81 ናቸው። እነዚህም 70ዎቹ ሊቃውንቶች ከዕብራይስጥ ቋንቋ ወደ ግሪክ የተረጎሟቸውን የብሉይ ኪዳን 54 መጻሕፍትን እነዚህም የሚያካትቱት ሄኖክ፣መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕና ዕዝራ ሱቱኤል፣ ሦስቱ መጽሐፈ መቃቢያን የሆኑትን ሲሆን ከሐዲስ ኪዳን ደግሞ 27 መጽሐፍትን ነው።


 

የቤተ ክርስቲያንዋ እምነት መርሆዎች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዶግማ ትምህርት የተመሠረተው ከመጽሐፍ ቅዱስ ከወጡትና በሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የተደነገጉትን የዶግማ ትምህርቶች ላይ ነው። ዋናዎቹም አምስቱ አእማደ ምሥጢራት ናቸው ።

እነዚህም፤

  1. ምሥጢረ ሥላሴ፣
  2. ምሥጢረ ሥጋዊ፣
  3. ምሥጢረ ጥምቀት፣
  4. ምሥጢረ ቁርባንና
  5. ምሥጢረ ትንሣኤ

ተብለው ይጠራሉ።

5.1 ምስጢረ ሥላሴ፣

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት የአምላክን ሦስትነትና አንድነት የሚያስረዳ ዋና የክርስትና እምነት መሠረት ነው። ይህ ዶግማ ረቂቅ ነው ይህ ትምህርት በእግዜአብሔር ካልተገለጸ በስተቀር በምርምር ብቻ የሚደረስበት አይደለም። “ከአብ በቀር ወልድን የሚያቅ የለም፣ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።” (ማቴ. 11፥27) የምናመልከው አንድ አምላክ በባሕሪይ አንድ አካል ሲሆን በግብር ሦስት አካላት ናቸው። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የምትቀበለው ይህን ትምህርት ነው “መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና ሦስቱም አንድ ናቸው።”

(1ኛ ዮሐ. 1፥5-7)

5.2 ምሥጢረ ሥጋዊ፣

ምሥጢረ ሥጋዊ የሚገልጽልን የአምላካችንን የድኅነት ሥራ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ መገለጹን ነው። ይህም ያስፈለገበት ምክንያት ህመማችን/ቁስላችን ኣዳኝ ሃኪም ስላስፈለገው ነው። (ሉቃ. 19፥10) ጨለማችን ብርሃን ስላስፈለገው ነው። (ማቴ. 4፥12-17፣ ዮሐ. 8፥12) ከባርነት ቀንበር ነጻ የሚያወጣ ስላስፈለገ ነው። (ገላ. 5፥1) በዚህ ጉዳይ ላይ ጸሎተ ሃይማኖትም አንዲህ ይላል፣ “ስለ እኛ ስለሰው ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበለው የእስክንድርያውን የቅዱስ ቄርሎስን የዶግማ ትምህርት ነው። “የወልድ አምላክነትን ባሕሪይ”  በሌላ አነጋገር ሁለቱ ባሕርያቶች “አምላክነትና ሰውነት”  ሲዋሀዱ የክርስቶስ ባሕርይ አንድ ብቻ ነው የሆነው። የቃሉና የሥጋ አንድነት በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ተዋሀደ ስለዚህ የሰውነት ባሕርይም ለአምላክነት የአምላክነት ባሕሪይም ለሰውነት ይገልጻል። በዚህ ንጹህ በሆነ ተዋህዶ “መለኮትና ሥጋ ያለመቀላቀል ያለመጠፋፋት አንድ ሆነዋልና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው” የኽውም ሰው የሆነው አምላክ መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዊ በኋላ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ ያለው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው”  ስለዚህ ስለ ሁለት ባሕሪያት መናገር አይቻልም። ስለዚህም በዮሐንስ ወንጌል እንዲህ  ተጽፏል “ቃል ሥጋ ሆነ፣ ጸጋንና አውነትንም ተመልቶ በኛ አደረ፣ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ዮሐ. 1፥14)

የቅዱስ አትናቲዮስ አገላለጽም “አምላክ ሰው ሆነ ይህም የሆነው የሰው ልጅ የሆነውን ወደ አምላክነት እንድንለወጥና የመለኮትን ባሕሪይ ተካፋዮች አንድንሆን ነው።” (2ኛ ጴጥ. 1፥4)

5.3 ምሥጢረ ክርስትና፣

ምሥጢረ ክርስትና ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት መግቢያ በርና የአምላካችንን የፀጋ ስጦታ የምንካፈልበት ነው። ምሥጢር የተባለበትም ምክንያት የማይታየውን ፀጋ በሚታየው የአምላክ ተግባር ስለምንቀበል ነው። (ማር. 16፥16፣ ዮሐ. 19፥34-35፣ ሐዋ. 2፥38) ። ጥምቀት ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚያስገባን የዕምነት በር ሲሆን ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም እንጂ በምንም ዓይነት የሚደገም አይደለም። (ኤፌ. 4፥4-7፣ ዮሐ. 3፥3-8)

5.4 ምስጢረ ቁርባን፤

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባደረገው በመጨረሻው እራት ላይ መሥርቶታል። እንዲህም ብሏል “በዚህ መታሰቢያ ስለ ሞቴና ስለ ትንሣኤዬ አስቡ” (ማቴ. 26፥26-30)

ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሏል “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፣ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን መታሰቢያዬን አድርጉት አለ።…” ስለዚህ ለእግዚአብሔር ሳይሰጥ ነገር ግን ስለ ሰዎች ተሰጠ በቁርባኑም ከኃጢያት ተገዢነት የሚያወጣንና ወደ አምላክ የሚያቀርበን ነው። (ዮሐ. 6፥53-57) ቁርባን በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ልቦና ውስጥ የገባና የመለኮትን ፀጋ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር የሚያገናኝ ሆነ።

5.5 ምሥጢረ ትንሣኤ፣

ምሥጢረ ትንሣኤ ዓለማዊ ከሆነው ሥጋችን ተለይተን ሞትን ድል አድርገን የምንነሣበትን በኋላም የምናገኘውን ዘለአለማዊ ሕይወት የሚገልጽ ምሥጢር ነው። ይኸውም የሚሆነው የጌታችንና የመድኃኒታች የኢየሱስ ክርስቶስ በክብር መምጣት ሲገለጽ ነው። ልክ እንደማንኛውም ፍሬ መጀመሪያ በስብሶ በኋላ እንደሚያፈራ ሁሉ። (ዮሐ. 12፥24 ፣ 1ኛ ቆሮ. 15፥36) ስለዚህ ሁላችን እንሞታለን ከዛም እንደገና እንነሣለን የመንግሥቱም ወራሾች ለመሆን። በጸሎተ ሃይማኖትም እንዲህ ይላል “የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፣ የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን።”


 

ሥርዓተ ቅዳሴ።

ቅዳሴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ አምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ ነው። ይህ ዋነኛ የሆነ የቤተ ክርስቲያኑ መንፈሣዊና ሃይማኖታዊነትን የሚገልጽ እንደ ወርቅ ማዕድን የሆነ ነው። ይህ አምላካዊ ግልጋሎት መግለጫ የሆነው የኢየሱስን በመስቀል ሞቱንና ትንሣኤውን የሚያከብርና ያለማቋረጥ ለሰው ልጆች የተሰጠውን የሕይወት ፍሬ ሁል ጊዜ የሚያሳይ ነው። ስለሆነም የቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴ ሁለት ዐበይት ነገሮችን ያካትታል፣

  1. ልዑል እግዚአብሔርን የሚያመሰግንና ስለማያልቅ የፀጋ ስጦታው ማክበር ነው።
  2. ቅዳሴ አዲስ መስዋዕት አይደለም ወይም የቀራንዮን መስዋዕትነት መድገም አይደለም። ይኸውም እውነተኛውና ንፁሑ የእግዚአብሔር በግ ለአንድ ግዜ ብቻ ተሰውቷል። ቅዳሴ የድኅነትን ሥራ የሚያረጋግጥ ማኅተም ነው። በዚህም የሚታየው ቤተ ክርስቲያን በአማኞቹ የሚገለጽ ነው (ካህናቱንና ምዕመናኑን ያቀፈ ነው) በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓተ ቅዳሴ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሚያንጸባርቅ መሆኑ ነው። በሁሉ የቅዳሴ ዓይነቶች ውስጥ ሙሉ ክርስቶስ የሚገለጽበት እንጂ የእርሱ ግማሽ አካል ብቻ የሚታይበት አይደለም።

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ውጭ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በእየሩሳሌም ከተማ ከተመሠረተችከ1, 500 ዓመት በላይ ነው። የኢትዮጵያና የእየሩሳሌም ግንኙነት የተመሰረተው ከ1,000 ዓ.ዓ. ጀምሮ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፣ ይኸም የንግሥት ሳባ ወደ ንጉሥ ሰለሞን ያደረገችው ጉብኝት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያልተቋረጠ ሆኖ በመቆየቱ በ34 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ሳለ በጋዛ በርሃ ሲጓዝ ሐዋርያው ፊሊጶስን አግኝቶ መጠመቁን በሐዲስ ኪዳን በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 26 እስከ 40 ተጽፏል። ከነዚህ ታላቅ ታሪኮች በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ የነበሩ የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎች፣ መንገደኞችና የእየሩሳሌም ከተማ ገዢዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስቲያን የማምለኪያ ቦታዎች እንዳሏት ያረጋግጣሉ።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን አፄ ዮሐንስ አራተኛው ቤተ ክርስቲያኑ የያዘውን ይዞታ በማስፋፋት የደብረ ገነት ገዳምን ሥራ አስጀመሩ ከእርሳቸው በኋላ በአፄ ምኒልክ ጊዜ ተጠናቀቀ። ከዚያን ጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት፣ገዳማትና ንብረቶች ተገዙ። በዚህ ከተማ ያላትን ይዞታ ጎልቶ አንዲታይ አድርጎታል።

በ20 ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የእየሩሳሌም ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ ተመሥርቶ በየዓመቱ በጥምቀት በገናና በትንሣኤ መንፈሣዊ ጉዞዎችን ወደ እየሩሳሌም ያዘጋጃል። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኦምነት ተከታዮች እነዚህን አመታዊ መንፈሣዊ ጉዞዎች ከተለያዩ የዓለም አገሮች ወደ ኢየሩሳሌም ያደርጋሉ።

በ1930 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. አፍሪካዊ የሆነ ቤተ ክርስቲያን የሚሹ ሰዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ምዕራቡ ዓለም እንዲመጣ አደረጉ።

በ1952 ዓ.ም.  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሪኒዳድ ቶቤጎና በጉያና ተቋቋመ ከዛም በመቀጠል በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ፣ በጃማይካ፣ በቤርሙዳ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ፣ ስዊዲን፣ በኖርዌ፡ በካናዳ፣ በአውስትራሊያ፣ በኒውዚላንድ፣ በምሥራቅ አፍሪካና፣ በደቡብ አፍሪካ ተቋቁሟል አሁንም በሌሎች የአውሮፓና የአፍሪካ ከተሞች እየተቋቋመ ነው።

እ.ኤ.አ. ከ1970 ዓ.ም. አጋማሹ ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በትምህርትና በስደት ከሀገራቸው በብዛት መውጣታችው በውጪ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ቁጥር እንዲጨምር አደረገው። ከ1972 ዓ.ም. ጀምሮ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የምዕራብ አገሮች ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ። የቤተ ክርስቲያኑና የምዕመናኑ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በተለይም እ.ኤ.አ. በ1992 ዓ.ም. በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያና አራት ሊቃነ ጳጳሳትና ብዛት ያላቸው ክህናት ከሀገር ተሰደው ወደ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ አሜሪካና ካናዳ ሲሄዱ የቤተ ክርስቲያኑ ቁጥር እጅግ እየበዛ ከመምጣቱም በላይ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ግልጋሎት ማግኘት የጀመረው ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን በማሠራት የተሠራውን በመግዛትና አቅም እስኪፈቅድ ድረስ በመከራየት ዕምነቱን ማጠናከር ቀጠለ። በዚህ መልኩ እየተጠናከረና እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታይ የሆኑትን ኢትዮጵያዊያንና ዕምነቱን የተቀበሉ የሌላ ሀገር ዜጎችንም አባላት በሚገባ ለማገልገል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. በዩናይትድ ሴት ኦፍ አሜሪካ ለ9 በካናዳ ለ4 ቆሞሳት የኤጲስ ቆጶስነት ማዕረግን ሰጡ።

በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት ።

እ.ኤ.አ. በ1972 ዓ.ም. በካናዳ የሚገኙ የዌስት ኢንዲስና የካሪቢያን አገሮች በአብዛኛው የጃማይካ ተወላጆች ጥረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን ጉባኤነት ደረጃ (ሚሽን) ተመሠረተ፤ እ.ኤ.አ. በ1984 ዓ.ም.የዚህ ጉባኤ አባላቶች ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳን ከጃማይካ ወደ ቶሮንቶ እንዲመጡ አደረጉ፤ ይህ በመሆኑ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ 425 ቫን ሮድ (425 Vaughan Road) በመባል በሚታወቀው መንገድ አንድ አነስ ያልች ቤት ተገዝቶ በካናዳ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን ተቋቋመ። ይህም ቤተ ክርስቲያን በቶሮንቶና በአካባቢው ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች ለሆኑ ኢትዮጵያዊያንንና የውጪ ዜጎችን ማገልገል ጀመረ። በዚያን ጊዜ የሚሰጠው አገልግሎት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ነበር። የምዕመናኑ ቁጥር መጨመርና የቦታው ማነስ ምክንያት ሌላ ቤተ ክርስቲያን መጨመር ግድ ሆነ። ስለዚህም 425 ቮን ሮድ ያለው የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ምዕመናንን ሲገለገሉበት ሌላ በቅድስት ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን እ.ኤ.አ. በ1991 ዓ.ም. ተመሠረተ። ይህ ቤተ ክርስቲያን ከ1991 ዓ.ም. እስከ  1996 ዓ.ም.  ማብቂያ ድረስ 40 ዌስትሙር ላንድ (40 Westmoreland Ave.) በሚገኝ  በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በኪራይ መልክ እሑድ እሑድ የቅዳሴ ሥርዓትን ረቡዕ አርብና ቅዳሜ ምሽት ላይ የጸሎት አገልግሎት ለምዕመናኑ ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በካናዳ ምድር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ንብረት በማፍራት በጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም. የ80 ታይኮስ ድራቭ ላይ ያለውን ሕንፃ በመግዛት ወደ እዚህ ስፍራ ለመዛወር ዝግጅት ላይ እንዳለ ከርሱ ቀጥሎ የሚገኘው ህንፃ ደግሞ ለሽያጭ ስለቀረበ በጥር ወር 1997 ዓ.ም. ግዢውን አጠናቆ የሁለት ሕንፃዎች ባለቤት በመሆን የ80 ታይኮስን ለቢሮና ለመንፈሣዊና ለማሕበራዊ ኑሮ ዝግጅቶች የሚሆኑ አንድ ትልቅና አንድ ትንሽ አዳራሽ ለግልጋሎት ሲበቁ የ84 ሕንፃ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያንነት ውስጡ ከታደሰ በኋላ በየካቲት 15 ቀን 1989 ዓ.ም. (February 22, 1997) በአራት ሊቃነ ጳጳሳት እነዚህም ብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ፣ በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ በ ታቦተ ሕጉ ተባርኮ የመጀመሪያው ቅዳሴ ተደረገ። የነበሩት ሕንፃዎች በቂ ባለመሆናቸውና የቤተክርስትያን ቅርፅ ያልነበረ ስለሆኑ ከሁለት ሺህ ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የተከተለና ሰፋ ያለ ቦታ ያለው ቤተክርስትያን ለመሥራት የመጀመርያ ፕላን ቀርቦ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የገንዘብ ስብሰባው ሥራ ጀመረ። በሁለት ሺህ ስድስት ዓ.ም. ኒኖ ሪኮ አርኪቴክት ድርጅት የሕንፃውን ፕላንና የማዘጋጃ ቤት ፈቃድ እንዲያገኝ ተመድቦ ሥራውን ጀምረ። ፈቃዱና የገንዘብ መሰባሰቡ ቀጥሎ  ኤፕሪል 18, 2010 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፡ ብፁዕ አቡነ መልከጼዲቅና በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተጣለ። ሥራውም በተቀላጠፈ ሁኔአታ ተጠናቆ በኅዳር ፰ ቀን ፪ሺህ፭ ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተባርኮ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት።

ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ስምንት በሆኑ ትላልቅ የካናዳ ከተሞች ቤተ ክርስቲያኖች አሉ እነርሱም፡ ቶሮንቶ፣ኦታዋ፣ ሞንትሪያል፣ዊኒፔግ፣ኤድመንተን፣ካልጋሪ፣ቫንኩቨርና ሃሊፋክስ ናቸው። በካናዳ ትላልቅ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ቁጥራቸው እንደ ቶሮንቶ ከተማ አይብዛ እንጂ በርከት ባሉበት ቦታዎች ሁሉ ዕምነታቸውን ይዘው ለመቆየትና ለልጆቻቸው ለማስተላለፍ ያልተቆጠበ ጥህረት እያደረጉ ነው ያሉት። ይኸም በመሆኑ እሑድ እሑድና በበዓላት ግዜ እየተሰባብሰቡ የፅዋ ማህበራት በማቋቋም ገንዘብ በማሰባሰብ በዐበይት በዓላት ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳን በመጋበዝ ቅዳሴና ሥጋው ደሙን እየተቀበሉ ከቆዩ በኋላ የቶሮንቶው ቤተ ክርስቲያን ባለንብረት መሆኑና ዋና ማእከል በመሆን በሌሎች ከተሞች እየተደራጁ ያሉት ክርስቲያን ወገኖች ካህን እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ እ.ኤ.አ. በ 1998 ዓ. ም. ለዊኒፔግ፣ ለካልጋሪና፣ ለኤድመንቶን ከተሞች ከኢትዮጵያ ካህናት እንዲመጡ ተደርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ተሸጋገሩ ከዛም በመቀጠል በኦታዋና በቫንኩቨር ሌሎች ካህናት መጥተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። በአሁኑ ወቅት በአሥር ከተሞች የሚገኙት ቤተ ክርስቲያናት የራሳቸው የሆነ ቤተ ክርስቲያን በመግዛት አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲገኙ የተቀሩት ሁለት ከተሞች የሚገኙት ቤተ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት በዝግጅት ላይ ናቸው።

በእየእሑዱና በተለያዩ ታላላቅ በዓላት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንዋ መንፈሣዊ አገልግሎትን ስትሰጥ ምዕመናኑ በታላቅ ተመስጦና አክብሮት በተለያዩ የአስተዳደር፣ በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች በመሳተፍና ግልጋሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በቶሮንቶ ከተማና በአካባቢዋ እስከ 45,000 ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ ይገመታል።ከነዚህ ነዋሪዎች በአብዛኛው በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት፣ባሕልና ታሪክ የሚፀና ነው። ስለዚህ ያላቸውን ዕምነትና ቅርስ በመያዝ ለትውልድም ለማስተላለፍ ያለባቸውን ኃላፊነት ተረድተው ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።

የመንበረ ብርሃን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ሰዓት በቁጥር ክ1, 600 በላይ የሆኑ የተመዘገቡ ቤተሰቦች አባላት አላት።


 

በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናት የሚሰጡት መንፈሣዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች።

የቅዳሴ ሥርዓት በየእሑዱና በበዓላት ቀናት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የጸሎት ፕሮግራም፣ የሰንበት ትምሕርት ቤት ፕሮግራም፣ የመዋለ ሕፃናት፣ ክርስቲያናዊ የቤተሰብ ምክር፣ መንፈሣዊ ምክር፣ ጋብቻ፣ የቀብር ሥነ ሥርዓት ።

ለአገሩ እንግዳ የሆኑትን ማስተናገድና ልዩ ልዩ ምክር መስጠት፡ በአካባቢው ካሉ ሌሎች የመንግሥትና የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፀረ ድህነት፡ ፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ፀረ አዕምሮ በሽታውችንና ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን በመዋጋት ዘመቻ ተካፋይ በመሆን ለምዕመናኑም ሆነ ለሚኖሩበት ሀገርና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቃሚነት የሚሰጡ ሥራዎችን ታከናውናለች።


 

ከሌሎች አብያተ ክርስቲይናት ጋር ያለ ግንኙነት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከመጀመሪያዎቹ የዓለም ኣብያተ ክርስቲይናት ማህበር መሥርች ሀገሮች አንዷ ነች። በካናዳም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን የካናዳ አብያተ ክርስቲያናት ማህበር እ.ኤ.አ. ከ 1985 ዓ.ም. ጀምሮ ቋሚ አባል ነች። ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ዋና የቦርድ አባል ሲሆኑ ሌሎች የቤተ ክርስቲይኗ አባላት በተለያዩ ኮሚቴዎችና ኮሚሽን ውስጥ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።