Contact Us

Use the form on the right to contact us.

You can edit the text in this area, and change where the contact form on the right submits to, by entering edit mode using the modes on the bottom right. 

(416) 781-4802

About Ethiopian Orthodox Tewahedo Church
--------------------------------------------------------------

Ethiopia, the land of Judeo-Christianity, is one of the most ancient predominantly Christian countries of the world. It is marked with a fascinating history, unique civilization, culture and religious life. The Book of Genesis recounts: “And the name of the second river is Ghion: the same is it that compasses the whole land of Ethiopia” (Geneses 2:13). The Psalmist David also says: “Let Ethiopia hasten to stretch out her hands to God” (Psalms 68:31).

አጽዋማት እና በዓላት

Back to All Events

የኢትዮጵያዊው ጻድቅ የአቡነ ሀብተማርያም በዓል

  • በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅድስት ማርያም ካቴድራል 80 Tycos Drive North York, ON, M6B 1V9 Canada (map)
Annual Feast of Abune Habte-Maryam.JPG

አቡነ ሀብተማርያም

፩ – የትውልድ ታሪካቸው

የቅዱስ አባታችን አቡነ ሀብተማርያም ትውልድ ሀገር የራውእይ የምትባል ምስራቃዊት ሀገር ውስጥ ሲሆን የኢትዮጵያ ንጉስ እስክንድር በነገሰ በሺ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምህረት ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚች ሀገር ውስጥ ነበር፡፡ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለጸጋ ነበር፡፡ በህጋዊ ጋብቻ ስሟ ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ ይህችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች፡፡ እነዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሀሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና % ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል እንዳለ” ማቴ. 16÷26፣ ማር. 10÷36፡፡ ለአንቺ ግን በሰማይ ፀንቶ መኖርን ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል የሚል ሀሳብ መጣባት፡፡ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነስታ በሌሊት ከቤት በመውጣት በሀገሯ አንፃር ትይዩ ወደ ሆነው ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሳማዎች፣ ከጦጦችና ከዝንጀሮዎች በስተቀር ምንም ምን ወደ ማይኖርበት በረሀ ደረሰች፡፡ በዚያም ደጃፏ ያልተዘጋ ትንሽ ዋሻ አገኘች፡፡ በዋሻው ውስጥም መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ የሚደግም ክቡር ባህታዊ አየች ባየችውም ጊዜ ደነገጠች እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሀት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፡፡ መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሀት መስላው ነበርና ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት፡፡ እሷም ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ሁሉ ትቼ መጥቻለሁ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድረበዳ መጣሁ አለችው፡፡ ይህም ባህታዊ በትህትናና በፈሪሀ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ አንድ ሰዓት ያህል ካሰበ በኋላ ምንኩስናስ የለሽም ነገር ግን በፍቅር በአንድነት ወደ ቤትሽ ወደ ህጋዊ ባልሽ በሰላም ተመለሽ የተፈቀደልሽን እነግርሻለሁ ከህጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል በህይወተ ስጋ ሳለ በፈጣሪው እግዚአብሔር ፍቃድ የብዙዎችን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል እንደ መላእክትም ክንፈ ፀጋ ተሰጥቶታል፤ በሰው አካል ከስጋ ሆኖ ሳለ በተመስጦ ወደ ሰማይ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነትን ምስጢር ያያል አላት፡፡ ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባህታዊው ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች የፈጣሪዬ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ አለች፡፡ ጥቂት ወራት ከቆየችም በኋላ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ፅጌረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ገፁ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች ይህ ህፃን በግንቦት ወርህ በ26 ቀን በተወለደ ግዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ ይህ ቅዱስ ህፃንም 40 ቀን በሞላው ጊዜ በኦሪትና በሉቃስ ወንጌል እንደተፃፈ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሙት ዘንድ ወደ ካህን አቀረቡት፡፡ ክህኑም ለክርስትና አባቱ አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተማርያም ብሎ ሰየመው ከዚህም በኋላ እናት አባቱም ተመለሱ፡፡ ይህ ቅዱስ ህፃን እግዚአብሔርን በመፍራት አደገ ከዕለታት አንድ ቀን ካህናቱ በቤተክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱእግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ እያሉ ሲፀልዩ ሰምቶ በልቡ ይህች ፀሎት በጣም ጥሩ መልካም ፀሎት ናት እኔ ይህችን ፀሎት መርጫታለሁ በዚህ ዓለም ከአሳች ህሊና በሚመጣውም ዓለም ከገሀነም እሳት እንድንድንባት አውቃለሁ አለ ስግደትንም እንደፈጣን ፈረስ ሩጫ ብዙ እስኪያልበው ድረስ ይሰግድ ነበር፡፡

 ፪  – አባታችን አቡነ ሀብተማርያም በሕይወት ሳሉ ካረፉም በኃላ ያደረጉት ተአምራት

አባታችን አቡነ ሀብተማርያም በሕይወት ሳሉም ሆነ ካረፉ በኋላ እጅግ ብዙ የሆኑ ተአምራትን አድርገዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም በጥቂቱ እንመልከት፡፡ የአቡነ ሀብተማርም አባት ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያምን ከዕለታት በአንድ ቀን የበግ ጠባቂ አደረጓቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን በኋላ ለብዙዎች ቅዱሳንና በዓለም ለሚኖሩ ምዕመናን በጎቹ ጠባቂ ያደርገው ዘንድ ወዶ መርጦታልና ያቀን እስኪደርስ ፈጣሪያችን ሀብትማርያምን ይጠብቀው ነበር በዚህም ዕለት በጎች ሲጠብቅ ብዙ የሚሆኑ የበጎች እረኞች እሸት ተሸክመው መጥተው ና እሸትን እንብላ አሏቸው፡፡ አባታችን አቡነ ሀብተምርያም ግን እኔስ አልበላም አሏቸው፡፡ እነርሱ እኛ ብላ ስንልህ ስለምን አትበላም አሉት አባትችንም ይህንን እሸት ከየት እንዳመጣችሁት ምንም እንደሆነ ስለማላውቅ ነው አላቸው (መጽሐፍ ኅጥእ ሰው እግዚአብሔርን የሚፈራውን ይንቀዋል ያቀልለዋል ብሎ እንደተናገረው) እረኞቹም አባታችንን በቁጣ ዓይን አዩዋቸው ብዙም ተቀጣጡባቸው ከዚህም በኋላ ከፊታቸው ተቀምጠው ያን ሰርቀው ያመጡትን እሸት መብላት ጀመሩ እሸቱንም በልተው ከጨረሱ በኋላ አባታችን ቅዱስ ሀብተማርያም በእነዚያን በግ ጠባቂዎችን የማንችለው ፅኑ ዝናብ መጥቷልና ወደየቤታችን እንግባ ከዚህም የምንጠጋበት ቤት ወይም ዋሻ የለምና አላቸው እረኞቹም ለኛ የማይታይ ለአንተ እንዴት ይታያል ብለው ተሳለቁባቸው፡፡

ቅዱስ ሀብተማርያምም የጥበብ አምላክ ልቡን በፀጋ መንፈስ ቅዱስ አበርትቶታልና እኔ የማውቀውን እናንተ አታውቁም ነገር ግን ወደየቤታችሁ ተመልሳችሁ በጊዜ ግቡ አሏቸው እነርሱም አንተ እራስህ ተመልሰህ ወደ ቤትህ ግባ እኛ ግን ፀሀይ ገና ቀትር እያለ ተመልሰን ወደ ቤታችን አንገባም አሉት፡፡ ይህንንም ባሉት ጊዜ በፍጥነት እየሮጠ በጎቹንም እያስሮጠ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ ወደ ቤቱም ከገባ በኋላ ፅኑ ዝናብ መጣ ንፋስም ነፈሰ እነዛም አረኞች ይህ ሁሉ በላያቸው ላይ እየተፈፀመ ሳለም አልሸሹም ነበር፡፡ እግዚአብሄርም ክፋታቸውን አስቦባቸዋልና በላያቸው ላይ የጥፋት ውሀ አወረደባቸው ሁላቸውም ይህንን የጥፋት ውሀ እስኪፈፀምባቸው ድረስ አልተነቃነቁም ነበርና ሁሉም አለቁ፡፡

በዚህም ሌሊት ቃል ከሰማይ ሶስት ጊዜ ሀብተማርያም  ሀብተማርያም ሲል ጠራው ይህም ህፃን አባቱ በአጠገቡ ተኝቶ ነበርና አባቱ የጠራው መስሎት አባቴ ሆይ አለሁ ሲል መለሰ፡፡ ይህንንም ማለቱ ቀድሞ በኤሊ ሊቀ ካህናት ጊዜ እንደተፈፀመ ሆኖበት ነው ሳሙ. 3÷3፡፡ እንደዚህም ሁሉ እግዚአብሔር ይህንን ህፃን ሀብተማርያም እያለ ሶስት ጊዜ ጠራው፡፡ ህፃኑም ሀብተማርያም ተነስቶ ታጥቆ እጅ ነስቶ እንደ ሳሙኤል ጌታዬ ባርያህ ይሰማል በል ተናገር አለው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከአሁን ጀምሮ ግን በግ ጠባቂዎች ከእርሻቸው ያልሆነውን ከሌላ እርሻ የሆነውን እሸት አምጥተው ብላ ቢሉህ አልበላም በላቸው፡፡ እናንተ ግን ብትወዱ ሄዳችሁ ብሉ በኋላ ግን ገሀነም ትገባላችሁ በእሳት ትቃጠላላችሁ በላቸው እንተን ግን ለሚሰሙ ለመረጥካቸው ቃሉን ትነግራቸው ዘንድ ከእኔ ጋር በሚስጢር ትነጋገር ዘንድ መርጬሃለሁ አለ፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ለቃልህ እታዘዝ ዘንድ እሺ ብያለሁ አለው የጠራውም ቃል ስሜንም በኋላ እነግርሃለሁ ነገር ግን የምልህን ቃልና ትዕዛዝ ጠብቅ አለው ዮሐ. 15÷10፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ዳግመኛ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ብዙም የበጎች እረኞች አብረውት ሳሉ አንድ የበግ ጠባቂ መጥቶ የአቡነ ሀብተማርያምን በትር በጉልበቱ ነጥቆት ሄደ፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ተከትሎ ያን በግ ጠባቂ በትሬን ለምን ትቀማኛለህ ቢለው ያም በግ ጠባቂ በጉልበቴ ነጥቄሃለሁ አለው፡፡ አባታችን አቡነ ሀብተማርያምም በጎቼን የምጠንቅበት በትሬን እንዳትወስድብኝ በህያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ ዳግመኛም አላምልህም እቋቋምህም ዘንድ ሀይል የለኝምና አለው፡፡ ያም በግ ጠባቂ በትእቢት እንቢ አልኩህ አለው አቡነ ሀብተማርያምም ከእንግዲህ ወዲህ አምልህ ዘንድ አልደግምም ነገር ግን በአንተ ላይ የሚደረገውን ሀይልና ተዓምር አንተው ታያለህና ብሎ ዝም አለ፡፡ ያም በግ ጠባቂ በህዋው በተሰቀለ ጊዜ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሀብተማርያም ሆይ ማረኝ እያለ ይጮህ ጀመር፡፡ ስመ እግዚአብሔርንና የፃድቁ ሀብተማርያምን ክብር ንቆ አቃሏልና ላዩ ታች ታቹ ላይ ቀኙ ግራው ግራው ቀኙ ሆኖ በአየር ተሰቅሎ ዋለ፡፡

በዚ የነበሩ የበግ ጠባቂዎችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው በጣም አደነቁ፡፡ እነርሱም አባታችን አቡነ ሀብተማርያምን ያደረጉትን ተአምር አይተዋልና እረኛውን እንዲምረው አሁንም አምላክን ስለወለደች ንዕድ ክብርት ስለምትሆን ስለ እመቤታችን ብለህ ማርልን አሉት ቅዱስ አባታችንም የሰቀልኩት እኔ ነኝን ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አማልኩት እንጂ የሃይሉንም ፅናት ያሳየው ዘንድ የሰቀለው እግዚአብሔር ነውና እርሱ ሁሉን ቻይና ይቅርባይ አምላክ ከተሰቀለበት ያውርደው አላቸው፡፡ አባታችንም ይህን ቃል በተናገረ ጊዜ የበግ ጠባቂው ከተሰቀለበት ወርዶ በእግሩ ቆመ በግ ጠባቂዎችም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለዘመዶቻቸውና ለወገኖቻቸው ያዩትን ተአምር ከመጀመሪያው  እስከመጨረሻው ተናገሩ፡፡ ይህንንም ተአምር የሀገሩ ሰዎች ሰምተው አደነቁ ይህ ታላቅ ፃድቅ ልጅ ነው በፊትም ቢሆን እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ እያለ ሲፀልይና  እንደፈጣን ፈረስ ኮቴ ፍጥነት ሲሰግድ ፊቱንም በድንጋይ እየመታ የክርስቶስን ህማማት አስቦ ሲጋደል አይተነዋል ብለው መሰከሩ፡፡ 

– ለአባታችን አቡነ ሀብተማርያም የተሰጣቸው ቃልኪዳኖች

አባታችን አቡነ ሀብተማርያም አራቱ ወንጌላት ከማንበብ ጋር ድካምና ተጋድሎ በበዛ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በቀኝና በግራ አስከትሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሲስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ በገሀድ ታየው ጌታችንም ወዳጅ ሀብተማርም ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን ባለው ጊዜ ከፈጣሪ ግርማ የተነሳ ደንግጦ ከመሬት ወደቀና እንደ በድን ሆነ ጌታችንም ክቡራት በሚሆኑ እጆቹ አንስቶ በፊቱ መንፈሰ ህይወትን አሳደረበት፡፡ ጌታችንም አቡነ ሀብተማርያምን ወዳጄ ሀብተማርያም ሆይ ድካምህና ገድልህ ሁሉ ለዘለዓለም መታሰቢያ ሊሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተፅፎልሃል ብዬ በእውንት እነግርሀለሁ ለአንተ ለወደድኩህና ለመረጥኩህ ለወዳጄ የማትዮስንና የማርቆስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሁሉ ተጭነህ  ወደ ምትሄድበት ቦታ ሁሉ የሚያደርስህ የብርሀን ሰረገላ እሰጥሀለሁ እንዳንተ ላሉ በዋሻ ከሚኖሩ ከመረጥኳቸው ቅዱሳን ትገናኝ ዘንድ ወደ ምስራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜን ወደ ደቡብ ትሄድበት ዘንድ የብርሀን ሰረገላ ሰጥቼሀለሁ ከሰው ፊት ከተሰወሩ ባህታዊያን ጋር ኑር ዳግመኛ የሉቃስንና የዩሀንስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ በእነርሱ ተጭነህ ስጋዬን ደሜን ለመቅመስ ኢየሩሳሌም ትደርስ ዘንድ የእሳት ሰረገላ ሰጥቼሀለሁ፡፡ በፀሎትህ አምኖ በጎ ስራ ለሚሰራልህ ሁሉ በህይወት ሳለህ ልብስህን በመስጠት ወይም ምግብ ወይም እግር በማጠብ ወይም እንጨት ሣር በማቅረብ ወይም ውሀ በመቅዳት በመርዳት ለደከሙ ሁሉ እምርልሀለሁ ብዬ ቃልኪዳን ሰጥቼሀለሁ፡፡ በህይወቱ ሳለ ለሚሻ መልካሙን ስራ ሁሉ አደርግለታለሁ ከሞትም በኃላ መንግስተ ሰማያትን አወርሰዋለሁ በባለሟልነት እቀበላለሁ ከአንተ ጋርም ደስ እሰኘዋለሁ፡፡ አንተ ከሞትክም በኃላ ስምህን የጠራውንና ዝክርህን የዘከረውን ሁሉ የሀብተማርያም አምላክ ሆይ ከጠላት እጅ አድነኝ ያለኝን በህሊና ያሰበውን በልቦና የወሰነውን እፈፅምለታለሁ ሰውን ከቸነፈር ከተቅማጥ እኮእሳት መቃጠል መብረቅ በረሀብ ከሞት እንዲያድን እንደ ሀዋርያት ስልጣን ቃልኪዳን ተሰጠው፡፡ አንትን ገድልህን ቃልኪዳንህን የናቀውንና ያቃለለውን ሁሉ ፍፁም መበቀልን እበቀለዋለሁ፡፡ ወደ መከራ ቦታ አወርደዋለሁ በበጎ ሳይሆን በመዓት አይን እመለከተዋለሁ፡፡ ጠላቶችህን ይበቀልልህ ወዳጆችህን ይጠብቅልህ ዘንድ መልዕክተኛዬ ቅዱስ ሚካኤልም ዘወትር አይለይህ የሰጠሁህን ቃልኪዳን እንዳልነሳህ በራሴ ማልኩልህ፡፡ እንደ ወዳጄ እንደ ፈቅጦርም በእናቴ በድንግል ማርያም አተምኩህ፡፡ ፈቅጦርን ከሰማዕታት ሁሉ አብልጬ እንደወደድኩት አንተንም ከመነኮሳት ሁሉ አብልጬ ወድጄሀለሁና ይህ የሰጠሁህ ቃልኪዳኔ ለዘላለም ይሁንልህ አለው፡፡

በፃድቁ አባታችን በአቡነ ሀብተማርያም በቃል ኪዳናቸው ፀንተን እንድንገኝ የልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!